የእግዚአብሔር ልዩ ፍቅር

ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ግንኙነት ከሌሎች ጋር ከሚኖርህ ግንኙነት የተለየ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአንተ ለየት ያለ ፍቅር አለው፡፡ ፍቅሩ በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ አይደለም (አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ የተመሠረተ አይደለም)፡፡ እግዚአብሔር የሚወድህ ስለ ወደደህ ብቻ ነው፡፡

“በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር ለእኛ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንደ እግዚአብሔር አንደ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስታሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደወደድነው አይደለም” (1ኛ ዮሐንስ 4፡9-10)

ቅልጥፍናህንና ሥራህን አይቶ አልወደደህም፡፡ እግዚአብሔር አሁን ከሚወድህ በላይ እንዲወድህ ሊያደርገው የሚችል ምንም ነገር ሠርተህ እንዲወድህ ልታደርገው አትችልም፡፡ ፍቅሩንም እንዲቀንስ ሊያደርገው የሚችል ነገር የለም፡፡ አንተ ራስህን እንኳን ከምትወደደው የበለጠ እርሱ ይወድሃል፡፡

እስካሁን በሕይወትህ የተለማመድከው በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተውን ፍቅር ይሆናል፡፡ በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ፍቅር አንተ በምታከናውነው ተግባር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሥራ፣ በቡድን፣ ወይም በግንኙነትህ ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረግህ “ትወደዳለህ”፡፡

ሕይወትህን ለክርስቶስ በመክፈትህ፣ ፍጹም ፍቅርንና ተቀባይነትን አግኝተሃል፡፡ ከዚህ ቀደም ከማንም ሰው ፍፁም ፍቅርንና ተቀባይነትን አግኘኝተህ የማታውቅ ከሆነ ነገሩን በውል መረዳት እጅግ ያስቸግርሃል፡፡ ግን ልንነግርህ የምንሻው እውነት ነው! የሚያሳዝነው ግን፣ እግዚአብሔር ይወደኛል የሚል ስሜት ዘወትር አይኖርህም፡፡ እንዲያውም ፍቅሩን ብቻ ሳይሆን፣ የመኖሩንም ጉዳይ ስትጠራጠር ራስህን ታገኘዋለህ፡፡ ምናልባት የተሸነፍህ ሊመስልህ ይችላል፡፡ አይሰማህ፡፡

እግዚአብሔር አዲስ ሕይወት ሲሰጥህ፣ የሚሰጥህ ሕይወት ውብና ማራኪ ሆና በሽቶ መዓዛም እንደተሸሞነሞነች አይነት አትመጣም፡፡ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን የጀመረው፣ የማይጣፍጥ ጠረን በሞላባትና በከብቶች ሽንት በረጠበች ግርግም ውስጥ ነበር፡፡ እርሱ የእውነተኛውን ሕወት ጣዕም አጣጥሞታል፣ ያም አንተ ከክርስቶስ ጋር የምታደርገው ጉዞ መዓዛም ያው ይሆናል፡፡ ምትሃታዊ ነገር ሳትጠብቅ፣ አብሮህ የሚኖረው እርሱ ሁልጊዜ አብሮህ እንደሚሆን የሰጠህ ተስፋ የታመነ ነው፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ “… በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ” (ኤርምያስ 31፡3)፡፡

“አንድ ሰው ሊያደርግ የሚገባው ብቸኛ ነገር ቀጣዩን ኪሎ ሜትር መጓዝ ነው፡፡” የሚል የዴንማርኮች አባባል አለ፡፡ ቀጣዩ እርምጃ እልህ አስጨራሽ መስሎ ሲታይህ በትዕግሥት እንድትራመድ የሚያስችልህ እግዚአብሔር እንደሚወድድህ ማወቅ ነው፡፡ “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፡፡” (ሮሜ 8፡38-39)

እምነታችን የሚያርፈው እግዚአብሔር ለእኛ ስለ ራሱ በገለጠልን ላይ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እርሱ ለእኛ ባለው ፍቅር እንድናምንና እንድንደገፍ ይፈልጋል፡፡

“እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱም በሚታመኑ ይደሰታል፡፡” (መዝሙር 147፡11)

“እነሆ፣ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፣ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፡፡” (መዝሙር 33፡18)

“እንደ ልቤ የሆነ ሰው”1 ተብሎ የተመሠከረለት፣ ንጉሡ ዳዊት፣ በእግዚአብሔር ፍቅር በመታመን፤ “እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና፡፡ ረዳቴ ሆይ፣ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፣ አምላኬ፣ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና፡፡” (መዝሙር 59፡16-17)

ኢየሱስ ለእኛ ያለውን የፍቅሩን ጥልቀት እንዲህ ሲል ገልፆታል፣ “አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ፡፡ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ፡፡ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈፀም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፡9-11)፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ መታዘዝ ሲያቅተንም እንኳን ይወደናል፡፡ ስንታዘዘው ግን፣ በፍቅሩ እንኖራለን፣ በፍቅሩም ደስ ይለናል፡፡

እግዚአብሔር ለአንተ ያለውን ፍቅር በመረዳት ለማደግ፣ በሚቀጠጥለው ሳምንት ጥቂት ጊዜ መድብና መዝር 103፣ ዮሐንስ 15 እና ዮሐንስ 4 አንብብና፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠባቸውን መንገዶች በማስታወሻ ላይ አስፍር፡፡

(1) የሐዋርያት ሥራ 13:22